በአገራችን ያለው ማህበረሰብ ለዳኛ እና ለፍርድ ቤት የሚሰጠው ቦታ በጣም የገዘፈ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች የፈለጉትን ነገር እንደፈለጉ የማስኬድ ስልጣንና መብት ያላቸው ይመስላቸዋል፡፡ ለዚያ ነው ዳኛ በተለምዶ ‘ከእግዚአብሔር ቀጥሎ የዜጋው እድል ፈንታ ወሳኝ ነው’ እየተባለ የሚወራው:: እውነታውና ህጉ ግን የሚያመለክተው ከዚህ የተለየ ነገር ነው፡፡ ህጋችን በግልፅ የሚያመለክተው ፍርድ ቤቶች በፍርድ አሰጣጥ ሒደት ላይ የሚጫወቱት ሚና በህጉ መሰረት ውስን መሆኑን ነው፡፡

በጥቅምት 2ዐ ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 33945 የወሰነው ውሳኔም ይህንን የሚያስረግጥ ነው፡፡

ጉዳዩ በአመልካች በአቶ ሳልህ ሁሴን እና በተጠሪ ደግፌ ደርቤ መሀከል ሲሆን ጉዳዩ የተጀመረውም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ነው፡፡ አመልካች ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ ተጠሪ በስማቸው ተመዝግቦ ያለውን ቁጥር 2ዐ7 እና 2ዐ6 የሆነ ቤት አስይዘው ብር 12,000.00(አስራ ሁለት ሺ) ተበድረው ቤቱን እንዳስረከቧቸው በስምምነት ወቅትም የማይንቀሳቀስ ንብረት መሸጥና መለወጥ ችግር ስለነበር ገንዘቡ የ1ዐ ዓመት መክፈያ ጊዜ ተወስኖለት በህዳር 2ዐ,1990 ማብቃቱን በተጨማሪ አመልካች በብድርና ዋስትና ውል ከአመልካች 5000.00 ተጨማሪ ብር መውሰዳቸውን የቤቱን የእድሳት ወጪዎችንም  አመልካች እንዲሸፍኑ ተጠሪ በውሉ መግለፃቸውን አስረድተው ተጠሪ በስምምነቱ መሰረት የብድሩን ገንዘብ በወቅቱ ካለመመለሳቸው በላይ የቤቱን ስም ንብረት በሽያጭ በማስተላለፍ የገቡትን ግዴታ ስላልፈፀሙላቸው አመልካች ብር 5,000.00 ጨምረው የቤቱ ስም በአመልካች እንዲዛወር ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

 

ፍ/ቤቱም የአመልካችን ክስና ማስረጃ መርምሮ በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተደረገ ውል የመያዣ ውል ሳይሆን የወለድ አግድ ውል ነው፣ ውሉ በተደረገበትም ወቅት የወለድ አግድ ግንኙነት የሚገዛው በአዋጅ ቁጥር 47/69 ስለነበር ይኸው አዋጅ የወለድ አግድ ውልን የሚከለክል በመሆኑ ውሉ ህገወጥ ስለሆነ ፈራሽ ነው በማለት ተዋዋዬች ወደ ነበሩበት ይመለሱ ሲል ወስኗል፡፡ ጉዳዩ ይግባኝ የቀረበለት ከፍተኛ ፍ/ቤትም የስር  ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት አለበት ምክንያቱም የበታች ፍ/ቤቶች ተጠሪ ቀርበው ባልተከራከሩበት እና የተጠሪ ዳኝነት በሌለበት ሁኔታ ቤቱን እንዲረከቡ መወሰናቸው አግባብ አይደለም በማለት ለሰበር ፍ/ቤት አቤቱታ አቅርቧል፡፡

ይህ ችሎትም ይህንኑ አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ከመረመረ በኋላ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ የሰጠው የአሁኑ አመልካች በግልፅ ባላመለከቱት እና ባልጠየቁት ዳኝነት ላይ ስለሆነ ይህ ደግሞ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 182(2) ድንጋጌ ስር የተመለከተውን የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የዳኝነት አሰጣጥ ከተጠየቀው ዳኝነት በተለየ ሁኔታ መሆኑ የስነ-ስርዓት ህግ ድንጋጌን ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ ስለሆነም በዚህ የሰበር ውሳኔ መሰረት ዳኝነት ባልተጠየቀበት ጉዳይ ላይ ፍ/ቤቶች ውሳኔ መስጠት እንደማይችሉ መገንዘብ እንችላለን፡፡

ተጨማሪ ጥያቄ አስተያየት ቢኖርዎት ያነጋግሩን ይጠይቁን

ኢሜይል  ፡-fikadu@ethiopianlaw.com

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢንቨስትመንት ጠበቃ፣ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ የጉዲፈቻ ጠበቃ፣ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ የፓተንት ጠበቃ፣ የኮፒራይት ጠበቃ፣ የታክስ ጠበቃ፣ የባንክ ጠበቃ፣ የኢንሹራንስ ጠበቃ፣ የፍቺ ጠበቃ፣ የቅጥር ውል ጠበቃ፣ የስራ ውል ጠበቃ፣ የውርስ ጉዳይ ጠበቃ፣ የኑዛዜ ጠበቃ፣ የቤተሰብ ጠበቃ፣ የንብረት ጠበቃ፣ የካሳ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ… ማግኘት ይችላሉ፡፡