ከዚህ በፊት ስለጡረታ ስምተው እንደሚያውቁ ጥርጥር የለኝም ነገር ግን እርሶ ከዚህ በፊት ጡረታ የሚለውን ቃል ሲሠሙ በመጀመሪያ ወደ አይምሮዎ የሚመጣው የመንግስት መስሪያ ቤት ነው ምክኒያቱም በፊት በፊት ጡረታ የሚከፈለው ሰው መንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ሲሠራ የቆየ ሠራተኛ ነው፡፡ አሁን ግን ከላይ በጠቀሰነው አዋጅ ቁጥር አንድ አዋጅ ወጥቷል ይኸውም የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠዎች የጡረታ መብት እንዲኖራቸው የሚደነግግ ነው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ከሰሞኑ ይሄ አጀንዳ የብዙ ሰዎች መነጋገሪያ ሆኗል እኔም ይህንን በመገንዘብ  ህጉ በአጭሩ ምን ለማለት እንደፈለገ ለማስቀመጥ እሞክራለው በንባብ ይከተሉኝ፡፡

በመጀመሪያ የግል ድርጅት ሰራተኛ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ብንመለከት የግል ድርጅት ሠራተኛ ማለት ማንኛውም በግል ድርጅት ውስጥ በቋሚነት በመቀጠር ደመወዝ እየተከፈለው የሚሠራ ሰው ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ህግ የሚመለከተው በግል መስሪያ ቤት ውስጥ በቋሚነት የተቀጠረን ሠራተኛ እንጂ በኮንትራት የተቀጠረን ሠራተኛ አይደለም፡፡

የአዋጁተፈፃሚነትወሰን

በአዋጅ ቁጥር 715/ዐ3 አንቀፅ 3 እና ተከታዮቹ ላይ እንደተደነገገው ይህ አዋጅ በዜግነት ኢትዮጵያ ለሆኑ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ይህ አዋጅ ከመፅናቱ በፊት በተቋቋሙ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ እቅድ ወይም ኘሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ያላቸው ሠራተኞች በነበራቸው እቅድ ወይም የኘሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነታቸውን ለመቀጠል ሊወስኑ ወይም በዚህ አዋጅ ስለሚሽፈኑበት ሁኔታ ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሀይማኖት ድርጅቶች እና የፓለቲካ ድርጅቶች ሠራተኞች እና መደበኛ ባልሆነው የስራ ዘርፍ የተሠማሩ ሠዎች በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ በዚህ አዋጅ መሠረት የጡረታ ሽፋን እንዲያገኙ እንደሚደረግ የአዋጁ አንቀፅ 3(2)(ለ) ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን ይህ አዋጅ የቤት ሠራተኞችንና መንግስታዊ የአለም አቀፍ ድርጅቶችና የውጭ መንግስታት ዲኘሎማቲክ ሚሲዮኖች ሠራተኞችን በተመለከተ ተፈፃሚነት አይኖረውም በሌላ አባባል እነዚህ ከላይ የጠቀሰናቸው ሠራተኞች  በዚህ አዋጅ ሽፋን አያገኙም፡፡

 

 

ምዝገባ

ማንኛውም የግል ድርጅት የተቋቋመበትን ህግ ፣ የግል ድርጅቱ ሠራተኛ ለመጀመያ ጊዜ ሲቀጠር የሞላውን የህይወት ታሪክ የተሠጠውን የቅጥር ደብዳቤ እና ሌሎች በኤጀንሲው የሚወሠኑ መረጃዎችን ለምዘገባ ለኤጀንሲው ማቅረብ አለበት፡፡ ምዝገባው ነባር የግል ድርጅቶችንና የግል ድርጅት ሠራተኞችን የሚመለከት ሲሆን ኤጀንሲው በሚወስነው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለምዝገባ መቅረብ አለበት፡፡ ነገር ግን ይህ አዋጅ ከጸና በኋላ የተቋቋመን የግል ድርጅት ወይም የተቀጠረ የግል ድርጅት ሰራተኛን የሚመለከት ሲሆን የግል ድርጅቱ በተቋቋመ ወይም ሰራተኛው በተቀጠረ በ6ዐ ቀናት ውስጥ መቅረብ አለበት፡፡ እነዚህ የምዝገባ ማስረጃዎች ተሟልተው የቀረቡ እንደሆነ የግል ድርጅቱ ወይም የግል ድርጅቱ ሠራተኞች የማህበራዊ ዋስትና መለያ ቁጥር ይሠጠዋል፡፡ ሆኖም የግል ድርጅቱ ወይም ሠራተኛው የታክስ መለያ ቁጥር ካለው ይኸው ቁጥር የማህበራዊ ዋስትና መለያ ቁጥር ጭምር ሆኖ እንዲያገለግል እንደሚደረግ የአዋጁ አንቀፅ 5(1) ይደነግጋል፡፡ ማንኛውም የግል ድርጅት የራሱንና የሠራተኛውን የምዝገባ መረጃ የተመለከት ለውጥ ሲያጋጥም ለውጡ ከተከሠተበት ቀን ጀምሮ በ 6ዐ ቀናት ውስጥ የተከሠተውን ለውጥ ከደጋፊ ማስረጃ ጋር አያይዞ ለኤጀንሲው በማቅረበ ማሣወቅ አለበት፡፡

 

የግልድርጅቶችሠራተኞችአገልግሎትጡረታፈንድመዋጮዋች

ለግል ድርጅቶች ሠራተኞች አገልግሎት ጡረታ ፈንድ በሠራተኛው ደሞዝ ላይ ተመስርቶ የሚደረገው መዋጮ እንደሚከተለው ነው

  • በግል ድርጅቱ 11%
  • በግል ድርጀት ሠራተኛው 7 %

እያንዳንዱ የግል ድርጅት የሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ከደመወዛቸው ቀንሶና የራሡን መዋጮ ጨምሮ ለሰራተኛው የወር ደሞዝ ለሠራተኞች ከተከፈለበት ቀን አንስቶ በ 30 ቀናት ውስጥ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ከሠራተኞቹ ደመወዝ ሊቀነስ የሚገባውን መዋጮ ሣይቀንስ የቀረ የግል ድርጅት ክፍያውን ራሱ ለመፈፀም ሀላፊ ይሆናል፡፡  ኤጀንሲው ወይም ውክልና የተሠጠው አካል ተገቢውን የጡረታ መዋጮ ለጡረታ ፈንድ ገቢ ሣያደርግ ከ 3 ወር በላይ የቆየ የግል ድርጅትን በባንክ ካለው ሂሣብ ላይ ተቀንሶ ገቢ እንዲሆን የማስደረግ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡

 

የአገልግሎትዘመንናየጡረታመውጫዕድሜ

የግል ድርጅት ሠራተኛ የአገልግሎት ዘመን መቆጠር የሚጀምረው በሰራተኛነት ከተቀጠረበት ቀን አንስቶ ነው፡፡ የአገልግሎት ዘመን የሚቆጠረው በሙሉ አመታት፣ በወራትና በቀናት ታሰቦ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ከመፅናቱ በፊት የግል ድርጅት ሠራተኛው የጡረታ እቅድ ወይም የኘሮቪደንት ፈንድ የነበረው ከሆነ የጡረታ እቅድ ፈንዱ ወይም የኘሮቪደንት ፈንዱ ለግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ ገቢ ሲሆን በአዋጁ አንቀፅ 1ዐ መሠረት ሊሽፈን በሚችለው የጡረታ መዋጮ መጠን አገልግሎት ይያዝለታል፡፡ ሰራተኛው ለመንግስት ሰራተኞች ጡረታ እቅድ የከፈለው መዋጮ ለግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ እቅድ በማዛወር በመንግስት መስሪያ ቤት የፈጸመው አገልግሎት እንዲያዝለት ይደረጋል፡፡ ለዚህ አገልግሎት አያያዝ የመንግስት ሰራተኞች ጡረታ ፈንድን የሚያስተዳድረው አካል የሰራተኛውን የግል መረጃና ለመንግስት ሰራተኞች ጡረታ ፈንድ የተከፈለውን የጡረታ መዋጮ ገንዘብ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ ማዛወር ይኖርበታል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የሠራተኛው በመንግስት መስሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ እቅድ ሽፋን ባላቸው የግል ድርጅቶች የተፈፀመ የአገልግሎት ዘመን በሙሉ ተደምሮ ይታሠባል፡፡

የጡረታመውጫእድሜ

በአዋጁ አንቀፅ 17 ላይ እንደተደነገገው የጡረታ መውጫ ዕድሜ የግል ድርጅት ሠራተኛው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀጠር በቅድሚያ የመዘገበውን የልደት ዘመን መሠረት በማድረግ 6ዐ አመት ይሆናል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኤጀንሲው በሚያቀርብለት ጥናት መሠረት በልዩ ሁኔታ በሚታዩ የሙያ መስኮች ከ 6ዐ አመት በላይ የሆነ የጡረታ መወጫ ዕድሜ ሊወሰን ይችላል፡፡ በከባድ ወይም ለጤንነትና ለህይወት አስጊ በሆኑ የስራ መስኮች ላይ ለተሰማሩ የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ከተጠቀሰው ማለትም ከ6ዐ አመት ያነሠ  የጡረታ መውጫ  ዕድሜ ሊወሰን ይችላል፡፡

ስለአገልግሎትጡረታአበልናደረጎት

በአዋጁ አንቀፅ 18 እና ተከታዩቹ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው ቢያንስ ለ 1ዐ አመት ያገለገለ ሠራተኛ የጡረታ መውጫ እድሜው በመድረሱ ከሰራ ሲሠናበት የአገልግሎት ጡረታ አበል አስከ እድሜ ልኩ ይከፈለዋል፡፡ እንዲሁም ለ2ዐ አመት ያገለገለ ሠራተኛ በራሱ ፈቃድ ወይም በአዋጅ ከተጠቀሡት ውጭ በሆነ ምክንያት አገልግሎት ካቋረጠ የጡረታ መውጫ እድሜው ሲደረስ የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ እድሜ ልኩ ይከፈለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ 25 አመት ያገለገለ የግል ድርጅት ሠራተኛ በራሱ ፈቃድ ወይም በአዋጁ ከተጠቀሱት ውጭ በሆነ ምክንያት አገልግሎት ካቋረጠ የጡረታ መውጫ እድሜው ሊደርስ አምስት አመት ከሚቀረው ጊዜ ጀምሮ እስከ እድሜ ልኩ የአገልገሎት ጡረታ አበል ይከፈለዋል፡፡ ነገር ግን እድሜው ለጡረታ ሲደረስ የጡረት መብት መከበሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ ሠራተኛ አገልግሎቱ የተቋረጠው በዲስኘሊን ጉደለት ምክንያት ከሆነ ከላይ የገለፅነው ድንጋጌ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡

ከላይ በጠቀሰናቸው ምክንያቶች መሠረት አገልግሎቱ የተቋረጠ የግል ድርጅት ሠራተኛ የጡረታ መውጫ እድሜው ሣይደርስ በጤና ጉድለት ምክንያት ለስራ ብቁ አለመሆኑ ከተረጋገጠ ይኸው ከተረጋገጠ ጊዜ ቀጥሎ ካለው ወር ጀምሮ የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ እችሜ ልኩ ይከፈለዋል፡፡ የሞተ እንደሆነም ከሞተበት ጊዜ ቀጥሎ ካለው ወር ጀምሮ ለተተኪዎች አበል ይከፈላል፡፡

የአገልግሎትጡረታአበልመጠን

ማንኛውም 1ዐ አመት ያገለገለ ሠራተኛ የሚከፈለው የጡረታ አበል መጨረሻ ባገለገለባቸው ሶስት  አመታት ውስጥ ይከፈለው የነበረው አማካይ ደሞዝ 3ዐ% ሆኖ ከ 1ዐ አመት በላይ ለፈፀመው ለእያንዳንዱ አመት አገልግሎት 1.25 % ተጨምሮ ይታሰባል፡፡ በዚህ መሠረት የሚወሠነው የአበል መጠን የግል ድርጅት ሠራተኛው በመጨረሻ ባገለግለባቸው ሥሰት አመታት ውስጥ ይከፈለው ከነበረው አማካይ ደሞዝ 7ዐ % ሊበልጥ አይችልም፡፡ ይህ ሠራተኛ በጤና ጉድለት ምክንያት ደሞዝ የሚያሰገኝ ማናቸውንም ስራ መስራት የማይችል በመሆኑ ከስራ ሲሠናበት የጤና ጉድለት ጡረታ አበል እስከ እድሜ ልኩ ይከፈለዋል፡፡

የአገልግሎትዳርጎት

ከ 1ዐ ዓመት ያነሠ አገልግሎት የፈፀመ የግል ድርጅት ሠራተኛ የጡረታ መውጫ እድሜው በመድረሱ ከስራ ሲሠናበት የአገልግሎት ዳረጎት ይከፈለዋል፡፡ የሚከፈለው ዳረጎት የግል ድርጅት ሠራተኛው ከስራ ከተሰናበተበት ወር በፊት ይከፈለው የነበረው 1.25% ወር ደሞዝ በአገለገለበት አመት ቁጥር ተባዝቶ ይታሰባል፡፡ከዚህም በተጨማሪ ይህ ሰራተኛ በጤና ጉድለት ምክንያት ለስራ ብቁ ባለመሆኑ ከስራ ሲሰናበት የጤና ጉድለት ዳረጎት ይከፈለዋል፡፡ የሚከፈለው ዳረጎት የሚታሰበው ከላይ በጠቀስነው መንገድ መሰረት ነው፡፡

ሰለጡረታመዋጮተመላሽነት

አንድ የግል ድርጅት ሠራተኛ ከ 1ዐ ዓመት ያላነሰና 2ዐ ዓመት ያልሞላ አገልግሎት ፈፅሞ በራሱ ፈቃድ ስራውን ከለቀቀ ወይም ከ 2ዐ አመት ያነስ አገልግሎት ፈፅሞ በአዋጁ ከተጠቀሱት ውጪ በሆነ ምክንያት ከስራ ከተሠናበት የአሠሪውን ድርሻ ሣይጨምር ሠራተኛው ራሱ ባዋጣው መጠን ብቻ የጡረታ መዋጮ ይመለሰለታል፡፡ ነገር ግን ከ 1ዐ አመት ያነሠ አገልግሎት ፈፅሞ በራሱ ፈቃድ ሥራውን ከለቀቀ ምንም አይነት ክፍያ አያገኝም፡፡

ስለጉዳትጡረታአበልናዳረጎት

በአዋጁ የተመለከተው ሌላው ነገር በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳትን በተመለከተ የሚሠጥ የጡረታ አበልን ሲሆን ይኸውም በአዋጁ አንቀፅ 27 እና ተከታዮች አንቀፅ ላይ በግልፅ ተዘርዝbል፡፡

በስራ ላይ በሚደርስ ጉዳት ምክንያት ከ 1ዐ % ያላነሰ ሊድን የማይችል ጉዳት ለደረሠበት የግል ድርጅት ሠራተኛ እንደሁኔታው የጉዳት ጡረታ አበል ወይም የጉዳት ዳረጎት ይከፈላል፡፡ አንድ ሠራተኛ በሰራ ላይ በሚደርስ ጉዳት ምክንያት ከ 1ዐ % ያላነሰ ሊድን የማይችል ጉዳት ደርሶበት ደመወዝ የሚያስገኝ ማናቸውንም ስራ መስራት የማይችል በመሆኑ ከስራ ሲሰናበት የጉዳት ጡረታ አበል መጠን እስከ ዕድሜ ልኩ ይከፈለዋል፡፡የሚከፈለው የጉዳት የጡረታ አበል መጠን የግል ድርጅት ሠራተኛው ጉዳቱ ከደረሠበት ወር በፊት ያገኝ ከነበረው መደበኛ የወር ደመወዝ  47 % ይሆናል፡፡ በዚህ መሠረት አበል ሊከፈለው የሚችል የግል ድርጅት ሠራተኛ በአገልግሎቱ ሊያገኝ የሚችለው አበል በጉዳት ሊያገኝ ከሚችለው የበለጠ ከሆነ የአገልግሎት ጡረታ አበል ይከፈለዋል፡፡

የጉዳትዳረጎት

አንድ የግል ድርጅት ሠራተኛ ከ 1ዐ% ያላነሰ ከስራ የመጣ ጉዳት ደርሶበት ሥራ ለመስራት የሚችል ከሆነ የጉዳት ዳርጎት ለአንድ ጊዜ እንደሚከፈለው የአዋጁ አንቀፅ 37(1) በግልፅ አስቀምጦታል፡፡ በዚሁ መሠረት የሚከፈለው የጉዳት ደረጎት መጠን የግል ድርጅት ሠራተኛው ጉዳት ከደረሠበት ወር በፊት ይከፈለው የነበረው መደበኛ የወር ደመወዝ 47 % በ 6ዐ ተባዝቶ የሚገኘው ሂሣብ በሠራተኛው ላይ በደረሰው ጉዳት መቶኛ ተባዝቶ ነው፡፡ ነገር ግን የግል ድርጅት ሠራተኛው አግባብ ባለው ህግ ወይም ህብረት ስምምነት መሠረት በአሠሪው የጉዳት ካሣ ወይም የመድን ክፍያ የሚያገኝ ከሆነ ከላይ የተጠቀሰው የጉዳት ደረጎት አይከፈለውም፡፡

 

የተተኪዎችጡረታአበልናዳረጎት

በአንቀጽ 39 እና ተከታዩቹ ላይ በግልፅ እንደተደነገገው ማንኛውንም የግል ድርጅት ሠራተኛ የአገልግሎት ወይም የጤና ጉድለት ወይም የጉዳት ጡረታ አበል በመከፈል ላይ እያለ ወይም ቢያንስ 1ዐ ዓመት አገልግሎ በስራ ላይ እያለ ወይም በሰራ ላይ በደረሠበት ጉደት ምክንያት ከሞተ ለተተኪዎች የጡረታ አበል ይከፈላል፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ የሟች ተተኪዎች እነማን ናቸው የሚለው ሲሆን በአዋጁ ላይ እንደተገለፀውም የሟች ተተኪዎች የሚባሉት፡፡

  1. ሚስት ወይም ባል
  2. ከ 18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ወይም አካል ጉዳተኛ ወይም የአዕምሮ በሽተኛ ልጅ ሲሆን ዕድሜው ከ 21 አመት በታች የሆነ
  3. ልጃቸው ከመሞቱ በፊት ሙሉ በሙሉ ወይም በአብዛኛው በሟች ድጋፍ ይተዳደሩ የነበሩ ወራሾች ናቸው፡፡

ከአስር አመት ያነሠ አገልግሎት ያለው ሠራተኛ በሰራ ላይ እያለ ከሞተ ከላይ በተራ ቁጥር 1 እና 2 ለተመለከቱት ተተኪዎች ዳረጎት ይከፈላቸዋል፡፡

ለተተኪዎችየሚከፈለውየጡረታአበል

ለሟች ሚስት ወይም ባል የሚከፈለው የጡረታ አበል ሟች ያገኝ ወይም ሊያገኝ ይችል የነበረው የጡረታ አበል 5ዐ% ሲሆን ለሟች ልጅ የሚከፈለው የጡረታ አበል ደግሞ 2ዐ% ይሆናል ለሟች ወላጆች ለእያንዳንዳቸው የሚከፈለው የጡረታ አበል ሟች ያገኝ ወይም ሊያገኝ ይችል የነበረው የጡረታ አበል 15% ይሆናል፡፡ ሆኖም ከወላጆች ሌላ ተተኪ ከሌላ 2ዐ % ይሆናል፡፡

ከላይ ባስቀመጥነው መሠረት ለተተኪዎች የሚከፈለው አበል ድምር ሟች ያገኝ ወይም ሊያገኝ ይችል ከነበረው አበል 1ዐዐ% ሊበልጥ አይችልም፡፡ ከተጠቀሰው መጠን በልጦ ከተገኘ ግን ከእያንዳንዱ ተተኪ አበል ላይ ተመጣጣኝ ቅናሽ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሰረት የተተኪዎች ጡረታ አበል ከተሰተካከለ በኋላ የተተኪዎች ብዛት ከቀነስ የአበሉ መጠን እንደገና ይስተካከላል፡፡

የጡረታአበልአከፍፈልናየመከፍያጊዜ   

የጡረታ አበል የሚከፈለው በየወሩ ይሆናል የአገልግሎት ጡረታ አበል መታሠብ የሚጀምረው የግል ድርጅት  ሠራተኛው  በዕድሜ ለጡረታ ብቁ ከሆነበት ቀጥሎ ካለው ወር መጀመሪያ ቀን አንስቶ ነው፡፡ የጤና ጉድለት ከሆነ ደግሞ ሰራተኛው በጤ ጎድለት ምክንያት መስራት የማይችል መሆኑ በህከምና ቦርድ ከተረጋገጠበት ቀጥሎ ካለው ወር የመጀመሪያ ቀን አንሰቶ ነው፡፡ እንዲሁም የጉዳት ጡረታ አበል መታሰብ የሚጀምረው ሠራተኛው በጉዳት ምክንያት መስራት የማይችል መሆኑ በህክምና ቦርድ ከተረጋገጠበት ቀጥሎ ካለው ወር የመጀመሪያ ቀን አንስቶ ነው፡፡ የተተኪዎች ጡረታ አበልን በተመለከተ መታሠበ የሚጀመረው ባለመብቱ ከሞተበት ቀጥሎ ካለው ወር መጀመያ ቀን አንሰቶ ነው፡፡

የዳረጎትአከፋፈልናየመክፈያጊዜ

ማንኛውም ዳረጎት የሚከፈለው በአንድ ጊዜ ነው፡፡ የአገልግሎት ወይም የጤና ጉድለት ዳርጎት ተከፋይ የሚሆነው የግል ድርጅት ሠራተኛው ከስራ ከተሠናበተበት ቀጥሎ ባለው ወር የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ነው፡፡ የጉዳት ዳርጎት ተከፋይ የሚሆነው የግል ድርጅተ ሠራተኛው ላይ ጉዳት ስለመድረሱና መጠኑን የሚገልፅ ማስረጃ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡

የይርጋጊዜ

ማንኛውም የውዝፍ ጡረታ አበል ወይም የዳርጎት ክፍያ ጥያቄ ከሶስት አመት በኋላ በይርጋ ይታገዳል፡፡ የጡረታ መዋጮ ተመላሽ ጥያቄ የግል ደርጅት ሠራተኛው የጡረታ መዋጮ ዕድሜ ከሞላ ወይም ከሞተ ከሶስት አመት በኋላ በይረጋ ይታገዳል፡፡ የይርጋ ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው በመብቱ መጠቀም ከሚቻልበት ቀጥሎ ካለው ቀን አንስቶ ነው፡፡ ነገር ግን ባለመብትነትን ለማረጋገጥ የተጀመረ የፍርድ ቤት ስርዓት እስከሚጠናቀቅ የወሠደው ጊዜ ማንኛውም የግል ድርጅት መረጃ የማስተላለፍ ግዴታውን በወቅቱ ባለመወጣቱ ያለፈው ጊዜ  እንዲሁም ኢጀንሲው የቀረበለትን የክፍያ ጥያቄ መርምሮ ለመወሰን የወሰደው ጊዜ በጠቅላላ በነዚህ በጠቀስናቸው ምክንያቶች የባከነ ጊዜ ለይርጋ አቆጣጠር እንደማይታሠብ የአዋጁ አንቀፅ 48/4/ በግልፅ ይደነግጋል፡፡

ተጨማሪ ጥያቄ አስተያየት ቢኖርዎት ያነጋግሩን ይጠይቁን

ኢሜይል  ፡-fikadu@ethiopianlaw.com

አግባብነትያላቸውተጨማሪህግመረጃዎችከማናቸውምኢትዮጵያዊጠበቃ፣ኢትዮጵያዊየፍቺጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊየቤተሰብጠበቃ፣ ኢንቨስትመንት ጠበቃ፣ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ የጉዲፈቻ ጠበቃ፣ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ የፓተንት ጠበቃ፣ የኮፒራይት ጠበቃ፣ የታክስ ጠበቃ፣ የባንክ ጠበቃ፣ የኢንሹራንስ ጠበቃ፣ የፍቺ ጠበቃ፣ የቅጥር ውል ጠበቃ፣ የስራ ውል ጠበቃ፣ የውርስ ጉዳይ ጠበቃ፣ የኑዛዜ ጠበቃ፣ የንብረት ጠበቃ፣ የካሳ ጠበቃ፣ማግኘትይችላሉ፡፡