ይርጋ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያውቃሉ? ይርጋ ማለት በአንድ ጉዳይ ላይ ባለመብት ወይም ከሳሽ መሆን የሚችል ሰው ጥያቄውን ለማቅረብ የሚችልበትን የጊዜ ገደብ የሚያሳይ የህግ መርሀ ነው፡፡ ከይርጋ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ህግ ውስጥ ያሉትን መሰረታዊ የፍትሀብሄር ይርጋ ድንጋጌዎች ከዚህ በታች ያገኟቸዋል፡፡

1. በውል ህግ ውስጥ

በፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 1845 መሠረት ውል እንዲፈፀም የሚጠየቀው ወይም ውል ካለመፈጸሙ የተነሳ የደረሰበትን ጉዳት የሚጠይቀው ግለሰብ መብቱን በህግ ለመጠየቅ የሚችለው በአስር ዓመት ግዜ ውስጥ ብቻ ነው፡፡

2. ከውል ውጪ የሚመነጭ ኃላፊነትን በተመለከተ

በፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2143 መሰረት ከውል ውጭ ባለ ኃላፊነት ላይ ተመስርቶ የሚቀርብ ክስ በሁለት ዓመት ይርጋ የሚታገድ ቢሆንም ጉዳዩ በወንጀል የሚያስቀጣ ሆኖ የወንጀሉ ይርጋ ዘመኑ ርዝመት ከሁለት ዓመት የበለጠ ከሆነ የካሳ ማቅረቢያው ጊዜ የወንጀሉን ይርጋ ግዜ የሚተካ ይሆናል፡፡

3. ውርስን በተመለከት

በውርስ ህግ ውስጥ የተለያዩ የይርጋ ደንቦች ተካተዋል፡፡

ይኸውም የኑዛዜውን መፍረስ የሚፈልጉ ወገኖች ይህን መብት የሚጠቀሙት ኑዛዜው ከተነበበ ወይም መነበቡን ካወቁና ተቃውሟቸውን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለውርስ አጣሪው ከገለፁ በኋላ ባሉት ቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ እንደሆነና በማናቸውም ምክንያት ቢሆን ግን ከአምስት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ጥያቄውን ማቅረብ እንዳለባቸው የፍትሐ ብሔር ህጉ ቁጥሮች 973 እና 974 ያስገነዝባሉ፡፡

በተጨማሪ ያለአግባብ የውርስን ንብረት በእጁ ካደረገው ሰው ላይ ንብረቱን ለማስመለስ የሚቀርበው ከሳሹ የውርሱ ንብርት በተከሳሹ መያዙን ባወቀ በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ከሳሽ ይህን ጉዳይ አወቀም አላወቀ ሟቹ ከሞተ ወይም ከሳሹ በመብቱ ለመስራት ከቻለበት ጊዜ አንሰቶ አስራ አምስት ዓመት ካለፈ በኋላ የውርስ ንብረት ለማስመለስ ጥያቄ ለማቅረብ አንደማይቻል የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 1ዐዐዐ ይገልፃል፡፡

ይሁን እንጂ በቅርቡ የሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት ባወጣው ውሳኔ መሰረት ባለንብረት የሆነ ሰው በውርስ ንብረቱ ላይ የሚያቀርበው የመፋለም መብት ይርጋ የሌለው ወይም በይርጋ የማይታገድ መሆኑን ገልጻል፡፡

4. በንብረት ህግ ውስጥ

ይዞታው የተወሰደበት ወይም በይዞታው ላይ ሁከት የተፈጠረበት ሰው ንብረቱ ይመለስልኝ ወይም ሁከቱ ይወገድልኝ ብሎ የሚያቀርበው ክስ ወይም አቤቱታ በሁለት ዓመት ይርጋ የተገደበ መሆኑ በፍትሐ ብሔር ህግ 1149(2) ተገልጿል፡፡

5. በአሰሪና ሠራተኛ ህግ ውስጥ

በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 377/2ዐዐ3 አዋጁ አንቀጽ 162 መሠረት የአንድ ሠራተኛ ውል የተቋረጠው ከህግ ውጪ ነው የሚል አቤቱታ በሚቀርብበት ጊዜ ሠራተኛው ወደ ስራው ለመመለስ የሚያቀርበው ጥያቄ ውሉ በተቋረጠ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ መሆን አለበት፡፡

የደሞዝ፣የትርፍ ሰአትና የሌሎች ክፍያዎች ጥያቄ ክፍያው በተቋረጠ በስድስት ወር ውስጥ መቅረብ አለበት፡፡

የሥራ ውል በመቋረጡ የተነሳ በሠራተኛውም ሆነ በአሠሪው የሚቀርብ ማንኛውም የክፍያ ጥያቄ የሥራ ውሉ በተቋረጠ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለበት፡፡

ከላይ ከተገለፁት ምክንያቶች ውጪ ሌሎች ከቅጥር ውል ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ማቅረብ  የሚቻለው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

6. በፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ህግ ውስጥ

በፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ህግ ውስጥ መብት ሊያሳጡ የሚችሉ የይርጋ ደንቦች ተካተዋል፡፡ በፍትሀብሄር ጉዳይ ላይ ፍርድ ወይም ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ የሚቀርብ ይግባኝ በ6ዐ ቀናት ውስጥ መቅረብ እንዳለበት የፍትሐ ብሔር ስነስርዓት ህግ አንቀጽ 323(2) ይገልፃል፡፡ በስራ ክርክር ውሳኔ ላይ ፍርድ ወይም ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ የሚቀርብ ይግባኝ ግን በ3ዐ ቀናት ውስጥ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

በተጨማሪም በይግባኝ ላይ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ የሚቀርብ የሰበር ማመልከቻ በ9ዐ ቀናት ውስጥ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም አንድ የተለየ ነገር እንዲፈፀም ፍርድ ቤቱ ከሚሰጠው ትእዛዝ በቀር ፍርድ እንዲፈፀም ማመልከቻ ቀርቦ 1ዐ ዓመት ከቆየና ይህ ጊዜ ካለፈ በኋላ ሌላ ማመልከቻ በማቅረብ ነገሩን ለማንቀሳቀስና ፍርድ እንዲዲፈፀም ለመጠየቅ አይቻልም፡፡

ተጨማሪ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካለዎት ያግኙን

 

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ታክስ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የወንጀል ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንብረት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የካሳ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የፓተንት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኮፒራይት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የስራ ፈቃድ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ጠበቃ … ማግኘት ይችላሉ፡፡