ይርጋ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያውቃሉ? ይርጋ ማለት በአንድ ጉዳይ ላይ ባለመብት ወይም ከሳሽ መሆን የሚችል ሰው ጥያቄውን ለማቅረብ የሚችልበትን የጊዜ ገደብ የሚያሳይ የህግ መርሀ ነው፡፡ ከይርጋ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ህግ ውስጥ የወንጀል ጉዳይን በተመለተ ያሉትን መሰረታዊ የይርጋ ድንጋጌዎች ከዚህ በታች ያገኟቸዋል፡፡

 

በወንጀል ህግ ውስጥ

የወንጀል ይርጋ በሁለት የተከፈለ ነው፡፡ ይኸውም የክስ ይርጋና የቅጣት ይርጋ ተብሎ  ይታወቃል፡፡

የክስ ይርጋ

ዐቃቤ ህግም ሆነ የግል ተበዳይ ወንጀል ፈጽሟል በተባለው ሰው ላይ ክስ ሊያቀርቡ የሚችሉበትን የጊዜ ገደብ የሚያስቀምጥ ሲሆን ዝርዝር አሰራሩ በወንጀለኛ ህግ አንቀጾች 216-222 ተገልጿል፡፡ በዚህ ህግ 217 እንደተገለፀው ከፍተኛውን ቅጣት ማለትም የሞት ፍርድ ወይም የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራትን ሊያስቀጡ የሚችሉ ወንጀሎች ተፈጽመዋል ከተባሉ ከ25 ዓመት በኋላ ክስ አይቀርብባቸውም፡፡

እንደ ወንጀሎቹ ክብደት፣ ከአምስት እስከ 2ዐ ዓመት በሚገኝ የይርጋ ዘመን የሚታገዱ የተለያዩ ወንጀሎች በዚህ አንቀጽ ውሰጥ ተካተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ በእስራት ሊያስቀጡ ወይም በገንዘብ መቀጫ ብቻ ለሚያቆሙ ወንጀሎች የክስ ማቅረቢያም የይርጋ ዘመን ሶስት ዓመት ነው፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 218 እንደተገለጸው ልዩ የይርጋ ዘመን አለ፡፡ ይኸውም በግል ተበዳዮች አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎችን በተመለከተ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ወንጀል የይርጋ ጊዜ ሁለት ዓመት ነው፡፡

 

የቅጣት ይርጋ

የቅጣት ይርጋ ከቅጣት አፈፃፀም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንድ ሰው ጥፋተኛ ነው ተብሎ ቅጣት ከተወሰነበት በኋላ ቅጣቱ ሳይፈፀም ቢቀር በሕግ የተመለከተው ጊዜ ካለፈ ቅጣቱን የማስፈፀም መብት እንደሚቀር የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 223 ይናገራል፡፡እንደ ወንጀሉ ክብደትና ቀላልነት የቅጣት ይርጋ በስላሳ ፣ በሃያ፣ በአስርና በአምስት ዓመት ሊወሰን እንደሚችል የዚህ ህግ ቁጥር 224(1) ዘርዝሮ ያስቀምጣል፡፡

 

የይርጋ ዘመን የሚያስከተለው ህጋዊ ውጤት

ይርጋ የባለዕዳው መከራከሪያ ነጥብ ነው፡፡ ህጉ ይህን መብት  አንስቶ የመከራከር ዕድል ለባለዕዳው ይሰጠዋል፡፡ ተጠቀምበት ብሎ ግን አያስገድደውም፡፡ በፍትሐ ብሔር ሰነ ስርዓት ሕጉ 244 እንደተመለከተው የይረጋ መብት ተጠቃሚ የሚሆነው ሰው ይርጋ ይደግፈኛል የሚለውን ክርክር የሚያነሳው በፍርድ ሂደት ውስጥ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ መልክ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱም ወደ ዋናው ክርክር ገብቶ ፍሬ ነገሩን ከመመርመሩ በፊት ክሱ በይርጋ ይታገዳል አይታገድም በሚለው ጭብጥ ላይ ብይን ይሰጣል፡፡ መቃወሚያው ተቀባይነት ካገኘ ዳኛው የነገሩን ፍሬ ነገር መመርመር አያስፈልገውም፡፡

ይርጋ በተከሳሹ ካልተነሳ ዳኛው በራሱ ተነሳሽነት እንዲያነሳ ሕጉ አይፈቅድም፡፡ ምክንያቱም ይርጋ ለባለዕዳው የሚያጎናጽፈው መብት “የሰነስርዓት መብት“ procedures Rights ሰለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ይርጋ በተከሳሹ እንደ መከራከሪያ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ካልተነሳ መብቱን እንደተወ ይገመታል፡፡

ዳኞች የይርጋ መከራከሪያን በራሳችው ተነሳሽነት ማንሳት   ባይችሉም በወንጀል ጉዳዮች ግን ተከሳሹ ባያነሳውም ዳኞች በይርጋ የታገደ የወንጀል ክስ ሲቀርብላቸው ማየት አይችሉም፡፡ በተመሳሳይ ቅጣቱ ሳይፈፀም የይርጋው ጊዜ ካለፈ አጥፊው ራሱ ባያነሳውም እንኳ አስፈፃሚው አካል ሊያነሳው እንደሚገባ በወንጀል ህግ 216(2) እና 223 (2) ተገልጿል፡፡

ተጨማሪ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካለዎት ያግኙን

 

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ታክስ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የወንጀል ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንብረት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የካሳ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የፓተንት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኮፒራይት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የስራ ፈቃድ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ጠበቃ … ማግኘት ይችላሉ፡፡