በአዲስ አበባ ውስጥ ከሰሞኑ የመነጋገሪያ አጀንዳ ውስጥ አንዱና ዋነኛው የነበረው አዲሱ የትራፊክ ደንብ  ነበር፡፡ ይህን ደንብ በተመለከተ ጥርት ያለ መረጃ ያለውም ሆነ መረጃ ሊሰጠኝ የሚችል ሰው ላገኝ አልቻልኩኝም ነበር፡፡ እንዲያውም ደንቡ የት እንደሚገኝ ጥያቄውን ያቀረብኩላቸው የትራፊክ ፖሊሶች የት እንደሚገኝ እንኳ ደንቡ የሚገኝበትን ቦታ አያውቁም ነበር፡፡ ኋላም ይህን ያውቃሉ ብዬ የገመትኳቸውን ኢትዮጵያዊ ጠበቆች የጠየቅኩኝ ቢሆንም እነርሱም ደንቡ የሚገኝበትን ቦታ አያውቁም ነበር፡፡ በደፈናው ግን አብዛኛው አዋጅ ወደሚገኝበት የብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ይጠቁሙኝ ነበር፡፡ ይህን ደንብ ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ትራፊክ ፖሊስ ካላወቀው ማን ሊያውቀው ይችላል በማለት ተገረምኩኝ፡፡ የኋላ የኋላ የዛሬ ሳምንት ደንቡ የወጣው በአዲስ አበባ መስተዳድር በኩል ሲሆን የሚገኘውም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ብቻ እንደሆነ ለመገንዘብ ችያለሁኝ፡፡

እስኪ ከራሱ ከአዋጁ እንጀምር፡፡ የአዋጁ መግቢያ እንደሚለው ይህ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ደንብ ሊወጣ የቻለው በከተማችን ውስጥ በትራፊክ አደጋ ምክንያት በሠው ሕይወትና ንብረት እንዲሁም በመስተዳዳሩ ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሠው ጉዳት በየዕለቱ ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ እንዲያዉም አሣሣቢ ደረጃ ላይ በመድረሡ ምክንያት እንዲሁም ከዚህም በተጨማሪ እያደገ ከመጣው የአለም ቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ በአሽከርካሪዎች ምክንያት ለአደጋ የሚያጋልጡ ሀኔታዎችን ለመቆጣጣር የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር በማስፈለጉ ምክንያትና ከዚህ ቀደም በነበሩ የትራፊክ ደህንነት ደንቦች ውስጥ ያልተካተቱና አዳዲስ የጥፋት አይነቶች እየተከሠቱ በመምጣታቸዉ የተነሳ አሁን ካለንበት የእድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣም ዘመናዊ የትራፊክ ስርዓትን የተከተለ ደንብ በማሥፈለጉ እንደሆነ ምክንያት ይህ የትራፊክ ደንብ ቁጥር 27/2ዐዐ2 ሊወጣ ችሏል፡፡

ስለ ትራፊክ ደንቡ አላማ ይሄንን ያህል ካልን ቀጥሎ የሚነሣው ጥያቄ ይህ ደንብ ተፈፃሚነቱ እስከ የት ድረስ ነው የሚለው ሲሆን የዚሁ የትራፊክ ደንብ አንቀፅ 3 እንደሚደነግገው ተፈፅሚነቱ በአዲስ አበባ ከተማ ክልል ውስጥ ብቻ ሆኖ በማናቸውም የትራፊክ አንቅስቃሴ ባለበት ቦታ ወይም የማቆሚያ ስፍራ ላይ ሁሉ ነው፡፡

የጥፋት አይነቶችና የቅጣት አወሣሠን

አንቀፅ 4 ስለጥፋትና የቅጣት አወሣሠን ይዘረዝራል፡፡ በዚህም መሠረት አንድ አግረኛ በ1956 ዓ.ም የወጣውን የትራንስፓርት ማሻሻያ ደንብ በአንቀፅ 61-65 ላይ የተደነገጉትን ጥሶ ከተገኘ ለሚደርስበት አደጋ ለጥፋቱ አንዳደረገው አስተዋፅኦ መጠን በሙሉ ወይም በከፊል ሀላፊ ይሆናል፡፡ ክልከላው በመጣሱም በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ መሠረት ይቀጣል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ጉዳት ያደረሰው አሽከርካሪ በ1956 ዓ.ም በወጣው የትራንስፖርት ማሻሻያ ደንብ አንቀፅ 83(2)(3) የተጠቀሱትን ግዴታዎች መፈፀም አለበት፡፡

የመጀመሪያ ቅጣት እርከን

አንቀፅ 4(3) ከመጀመሪያ እርከን - ሠባተኛ እርከን ድረስ የሚቀመጡ ጥፋቶች የሚያስቀጡትን የቅጣት መጠን /ብር/ ይደነግጋል፡፡ ከዚሁ ደንብ ጋር የተያያዘው ሠንጠረዝ ሀ ደግሞ የጥፋቶቹን አይነት ይዘረዝራል:: በዚህም መሠረት ቀጥሎ የተዘረዘሩት ጥፋቶች በደንቡ መሠረት የመጀመሪያ እርከን ጥፋቶች ሲሆኑ የቅጣት መጠናቸውም 6ዐ ብር ነው፡፡

 1. ተሽከረካሪን ያለአግባብ የጎተተ
 2. መንገድ ላይ እንሰሳትን የነዳ
 3. የተሟላ የጭነት ማቀፊያ /ስፓንዳ/ የሌለው ተሽከርካሪ
 4. የጥሩንባ ድምፅ ያለአግባብ (በማይገባ ቦታ) የተጠቀመ
 5. በትርፍ ጭነት ላይ ምልክት ያላደረግ
 6. ከፍተኛ ጭስ የሚያጨስ ተሽከርካሪ የነዳ
 7. የለማጀ ምልክት ሣይለጥፍ እና ባልተወሠነ ቦታ እንዲሁም ሠአት ተሽከርካሪ መንዳት ያስተማረ
 8. ለሀዘን ከሆነ ሣያሰፈቅድ ወይም ተክሎ ወዲያው በአቅራቢያው ላለው የፖሊስ ጣቢያ ሣያሳውቅ ድንኳን በመንገድ ላይ ያቆመ
 9. መንገድ ላይ ተሽከርካሪ ያሣጠበ
 10. ለእግረኛ ክልክል በሆነ መንገድ ላይ ያቋርጠ
 11. ለማቋረጥ ከተፈቀደለት ዉጪ በቀለበት መንገድ ላይ ያቋርጠ
 12. ለእግረኛ ከተዘጋጀ መንገድ ዉጪ በተሽከርካሪ መንገደ ላይ የተጓዘ
 13. በመንገድ ላይ የንግድ ሥራ የሰራ
 14. የመጀመሪያ ሕክምና ኪት በተሽከርካሪው ያልያዘ
 15. ውሀ በእግረኛ ላይ የረጨ
 16. በብልሽት/ በግጭት ምክንያት መንገድ ላይ የወደቁ የተሽከርካሪ ስብርባሪዎችን ያላፀዳ

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ጥፋቶች ህጉ የመጀመሪያ እርክን ጥፋቶች ብሎ ያስቀመጣቸው ሲሆኑ ማንኛውም አሽከርካሪ ሆነ እግረኛ እንዚህን ጥፋቶች አጥፍቶ ቢገኝ 6ዐ ብር ቅጣት የሚቀጣ ይሆናል፡፡

የሁለተኛ ቅጣት እርከን

የሚከተሉት የጥፋት አይነቶች የሁለተኛ ቅጣት እርከን ላይ የሚቀመጡ ጥፋቶች ሲሆኑ ማንኛውም አሽከርከሪ ሆነ እግረኛ እንዚህን ጥፋቶች አጥፍቶ የተገኝ እንደሆነ 8ዐ ብር የሚቀጣ ይሆናል ፡፡ ጥፋቶቹም

 1. ወደማይሄድበት አቅጣጫ ምልክት ያሳየ
 2. ምልክት ሣያሳይ ተሽከርካሪ ካቆመበት ቦታ ያንቀሣቀሠ ወይም ያቆመ
 3. በተሽከርካሪ የወጪ አካል ላይ ሠው የጫነ
 4. የቀስት አቅጣጫ የለቀቀ
 5. የቀኙን ጠርዝ ሳይዝ በዝግታ የነዳ
 6. ያለአግባብ ወደ ኋላ ያሽከረከረ
 7. ለአላፊ ተሽከርካሪ ቅድሚያ የከለከለ
 8. በተከለከለ ቦታ በትራፊክ ደሴት እንዲሁም በድልድይ ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ
 9. በትራፊክ ምልክት መብራት አጠገብ ተሽከርካሪ ያቆመ
 10. በባቡር ሀዲድ አጠገብ ተገቢውን ጥንቃቄ ያላደረገ
 11. መብራት እያለው በማብሪያ ጊዜ ሣያበራ ያሽከረከረ
 12. የመንጃ ፍቃድ /የአሽከርካሪነት ብቃት ማረጋገጫ ሳይዝ ያሽከረከረ፣ ያላሳደሰ
 13. ያለፈቃድ ተሽከርካሪ መንዳት ያሰተማረ
 14. ሠሌዳው የተደመሠሠ ወይም የተቆረጠ ወይም የተሸፈነ ተሽከርካሪ ያሽከረከረ
 15. ከተፈቀደው ፍጥነት በታች ያሽከረከረ
 16. በእጅ የሚገፋ ወይም የሚሣብ ጋሪ በዋና መንገድ ላይ የገፋ ወይም የሳበ
 17. የጉዞ መስመር ጠብቆ ያላሽከረከረ

Zስተኛ የቅጣት እርከን

የጥፋት አይነቶች

 1. በ25 ሜትር ርቀት ምልክት ሳያሣይ የተሽከርካሪውን አቅጣጫ የቀየረ
 2. የሚከለከል ምልክት የጣሠ
 3. የሚያስገድድ ምልክት የጣሠ
 4. ደሴት በግራ ያቋርጠ
 5. በጠባብ መንገድ ላይ ያቆመ
 6. በመታጠፊያ መንገድ ላይ ያቆመ
 7. የመንገድ አከፋፋይ ደሴት/መስመር ያቋርጠ
 8. የጭንቅላት መከላከያ /ሄልሜት/ ሣያደርግ ሞተር ሣይክል ያሽከረከረ ወይም ከኋላ ሠው ያፈናጠጠ
 9. የተበላሸ ተሽከርካሪ መንገድ ላይ የጠገነ
 10. ከተወሠነለት መቀመጫ ወይም የጭነት ልክ በላይ የጫነ
 11. በአሽከርካሪው ላይ የተጫነውን ጭነት በሚገባ ያላሠረ ወይም ያላለበሠ
 12. ሳያስፈቅድ እይታን የሚከለክሉ መጋረጃዎችን ወይም ተለጣፊ ላስቲክ የለጠፈ
 13. አፈር፣ አሸዋ፣ ድንጋይና የመሳሰሉትን ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ያራገፈ ወይም እንዲራገፍ ያደረገ
 14. ሌሎች የትራፊክ ፍሰትን የሚያሠናክሉ ድርጊቶችን የፈፀመ
 15. በተሽከርካሪው ላይ ተገቢ ያልሆነ አካል የጨመረ
 16. የተለጣፊ ምልክት /ቦሎ/ ያልለጠፋ
 17. የአሽከርካሪን እይታ የሚከለክል ማንኛውም አይነት ማስታወቂያ ወይም ሌላ ነገር መንገድ ዳር ወይም መሀል ላይ የተከለ ወይም የገነባ
 18. ለተለያዩ ተግባራት መንገደ ቆፍሮ ወደነበረበት ሳይመልስ የቀረ

 

እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው የጥፋት አይነቶች ህጉ 3ኛ እርከን ላይ ያስቀመጣቸዉ ሲሆኑ ማንኛዉም አሽከርካሪም ሆነ ግለሰብ ጥፋቱን ፈፅሞ የተገኝ እንደሆነ በትራፊክ ደንቡ አንቀፅ 4/3/ሐ/ መሠረት 1ዐዐ ብር ይቀጣል፡

አራተኛ የቅጣት እርከን

እነዚህ የቅጣት አይነቶች የትራፊክ ደንቡ በአራተኛ የቅጣት አርከን ላይ ያሰቀመጣቸው እያንዳንዳችው የ12ዐ ብር ቅጣት የሚያስቀጡ ናቸው፡፡

 1. ተሽከርካሪ በአንቅስቃሴ ላይ እያለ ተሣፋሪ የጫነ ወይም ያወረደ
 2. በተሽከርካሪ መግቢያ ወይም መዉጫ በር ላይ የቆመ
 3. አመታዊ የተሽከርካሪ ደህንነት ምርመራ ያላደረገ
 4. ግልፅ ጉድለት ያለው ተሽከርካሪ ያሽከረከረ
 5. በትራፊክ ደሴት ላይ ያሽከረከረ
 6. ከተማ ውስጥ ከባድ መብራት /ባውዛ/ የተጠቀመ
 7. ያለማንፀባረቂያ ምልክት የተበላሸ ተሽከርካሪ በመንገድ ላይ ያቆመ
 8. ከ2 ሠአት በላይ ከባድ ተሽከርካሪ በመንገደ ላይ ያቆመ
 9. በሠንሠለት የሚሽከረከርና በሠአት ከ1ዐ ኪ.ሜ በታች የሚጓዝ ልዩ ተሽከርካሪ መንገድ ላይ ያሽከረከረ
 10. በአውቶቢስ መቆሚያ ስፍራ ላይ ሌላ ተሽከርካሪ ያቆመ
 11. ከባድ ተሽከርካሪ ላይ ከኃላ አንፀባራቂ ምልክት ሣይለጥፍ ያሽከረከረ

አምስተኛው የቅጣት እርከን

ከዚህ በታች የተቀመጡት ጥፋቶች የትራፈክ ደንቡ አንቀፅ 4/3/ሠ/ ላይ አምስተኛ እርከን የጥፋት አይነቶች ብሎ ያስቀመጣቸው ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ጥፋቶች የ14ዐ ብር መቀጫን ያስከትላሉ ጥፋቶቹም የሚከተሉት ናቸው፡፡

 1. ደረጃውን ባልጠበቀ መንጃ ፈቃድ /የአሽከርከሪነት ብቃት ማረጋገጫ ያሽከረከረ
 2. መስቀለኛ መንገድ ላይ ቅድሚያ ያልሠጠ
 3. ቅደሚያ መሠጠት ሲገባው የከለከለ
 4. የትራፈክ መብራት ወደቀኝ መታጠፍ ለሚፈቅድለት ተሽከርካሪ መንገድ የዘጋ
 5. አለአግባብ ተሽከርካሪ የቀደመ
 6. የተሽከርካሪ በር ከፍቶ ያሽከረከረ
 7. በህግ ከተወሰነው ከፍታ ርዝመት ወይም ስፋት ውጭ ጭነት የጫነ
 8. የእግረኛ መንገድ ለተለየ አገልግሎት ያዋለ
 9. ከሀዘን በስተቀር ያለፓሊስ ፈቃድ በመንገድ ላይ ድንኳን የተከለ
 10. የፓሊስ ወይም በጎ ፈቃደኛ ትዕዛዝ ያልፈፀመ
 11. ዕደሜያቸው ከሠባት አመተ በታች የሆኑ ህፃናት በተሽከርካሪ ጋቢና አሣፍሮ ያሽከረከረ
 12. ህጋዊ ስልጣን ካለው አካል ፈቃድ ሣያገኝ በመንገድ ትራፊክ ምልክት የተጠቀመ

ስድስተኛ የቅጣት እርከን

እዚህኛው እርከን ላይ የሚቀመጡት ጥፋቶች ህጉ ከባድ ብሎ ያስቀመጣቸው የትራፊክ ደንብ የጥፋት አይነቶች ሲሆኑ እያንዳንዳቸውም የ16ዐ ብር ቅጣት ያስከትላሉ፡፡ ጥፋቶቹም እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡

 1. ሠክሮ ፣ አደንዛዥ ዕፅ ወይም ጫት ውሰዶ ወይም ሺሻ አጭሶ ያሽከረከረ
 2. የጆሮ ማዳመጫ /ኤር ፎን/ ጆሮው ውስጥ በመክተት ሬድዮ እያዳመጠ ወይም ሞባይል እያናገረ ያሽከረከረ
 3. ሞባይል ስልክ በእጁ ይዞ ወይም ተDከርካሪው ላይ ገጥሞ እያናገረ ማንኛውንም አይነት ተሽከርካሪ ያሽከረከረ
 4. የተሽከርካሪ የመቀመጫ ቀበቶ ሣያስር ወይም ሌሎች እንዲያስሩ ሣያደረግ ያሽከረከረ
 5. ሬዴዮ፣ ቴኘ ፣ ሲዲ በከፍተኛ ደምፅ ከፍቶ እያዳመጠ ያሽከረከረ
 6. የመንጃ ፈቃድ / የአሽከረካሪ ብቃት ማረጋገጫ ሳይኖረዉ ያሽከረከረ
 7. የመንጃ ፈቃድ/ የአሽከርካሪነት ብቃት ማረጋገጫ ለሌለዉ ሰዉ እንዲያሽከረክር የሰጠ
 8. ለእግረኛ ቅድሚያ ያልሰጠ
 9. ቀይ የትራፊክ መብራት የጣሰ
 10. በህግ ከተወሠነው ፍጥነት በላይ ያሸከረከረ
 11. የእሳት አደጋ ተሽከርካሪ ዉሀ መሙያ ቦታ ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ
 12. ለአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ ቅድሚያ ያልሰጠ
 13. በእሳት አደጋ ወይም ሆስፒታል በር ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ
 14. በእግረኛ መንገድ ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ
 15. በእግረኛ ማቋረጫ ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ
 16. ምንም መብራት ሣይኖረው ያሽከረከረ
 17. በተከለከለ መንገድ ወይም አቅጣጫ  ያሽከረከረ
 18. መሀል መንገደ ላይ ተሳፋሪ ወይም ጭነት የጫነ ወይም ያወረደ
 19. የትራፊክ አደጋ ፈፅሞ ቦታው ላይ ያልቆመ
 20. ቴሌቪዥን ወይም ቪዲዩ ተሽከርካሪ ውስጥ እያየ ያሽከረከረ
 21. በትራፊክ መብራት ላይ ወይም በመሰቀለኛ መንገድ ላይ ወይም ሌላ ማናቸውም መንገድ ላይ በልመና ላይ ለተሠማሩ ሠዎች ገንዘብ ያሠጠ ወይም የሠጠ ወይም ማንኛውንም አይነት ግብይት ያረገ ወይም ያሰደረገ
 22. የመንገድ ትራፊክ ምልክት ያበላሸ የሚያስተላልፈውን ይዘት የቀየረ ወይም ከተተከለበተ ቦታ ያዞረ ወይም በመንገድ ምልክት ላይ ማስታወቂያ የለጠፈ
 23. ተሽከርካሪው ከተፈቀደለት አገልግሎት ውጪ ለሌላ አገልግሎት የተጠቀመ

ሠባተኛ የቅጣት እርከን

በትራፊክ ደንቡ አንቀፅ 4/3/ሰ/በሠባተኛ የቅጣት እርከን ላይ የተቀመጡት የጥፋት አይነቶች ህጉ በተለየ ሁኔታ እጅግ በጣም ከባድ የትራፊክ ደንብ ጥፋት ብሎ ያስቀመጣቸው ሲሆኑ የቅጣት መጠናችውም ከ3ዐዐ.ዐዐ ብር ጀምሮ እንደየጥፋቱ አይነት አስከ ብር 7ዐዐ.ዐዐ የሚያስቀጡ ጥፋቶች ናችዉ፡፡ እነሡም በብር 3ዐዐ.ዐዐ የሚያስቀጡ ጥፋቶች

 1. በቂ ርቀት ሣይጠብቅ በማሽከርክር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሠ
 2. ያለአግባብ ተሽከርካሪን ወደ ኋላ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ በብር 350.00 የሚያስቀጡ ጥፋቶች
 3. ማንኛዉም አሽከርካሪ ተሽከርካሪን ካቆመበት ያለጥንቃቄ ሲያነሣ፣ ተሽከርካሪን ደርቦ ሲታጠፍ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነና እንዲሁም ተሽከርካሪን በመገልበጥ በራሱ ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ለዚሁ ጥፋት ብር 35ዐ.ዐዐ ቅጣት የሚቀጣ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ህጉ 4ዐዐ.ዐዐ ብር የሚያስቀጡ ጥፋቶች ብሎ የዘረዘራቸዉ የጥፋት አይነቶች አሉ፡፡ እነሱም

 1. የተሽከርካሪ መሪ ያለአግባብ ተጠቀሞ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሠ
 2. ከመጋቢ መንገድ አቅጣጫ ተDከርካሪ እያሽከረከረ ወጥቶ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ
 3. ተሽከርካሪን እያሽከረከረ ከመንገድ ወጥቶ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ
 4. ለሌላ ተሽከርካሪ በተገቢዉ ቦታ ላይ ቅድሚያ በመከልከል በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ
 5. ተሽከርካሪ እያሽከረከረ በቀኝ በኩል በመቅደም በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሠ
 6. ያለደረጃ የአሽከርካሪነት ብቃት ማረጋገጫ ይዞ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ
 7. የአደጋ ተካፋይ ሆኖ ያመለጠ ወይም ወደሚመለከተው አካል ያልቀረበ ናቸዉ፡፡

ከዚህ በታች የምንመለከታቸው ደግሞ ህጉ የ5ዐዐ.ዐዐ ብር ቅጣት ያስከትላሉ ብሎ ያስቀመጣችው የጥፋት አይነቶች ሲሆኑ ማንኛውም ሠው እነዚህን ጥፋቶች አጥፍቶ የተገኘ እንደሆነ የ5ዐዐ ብር ቅጣት ይጠብቀዋል ፡ የጥፋቶቹም አይነት

 1. ከተፈቀደለት ፍጥነት በላይ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ
 2. የሚያስገድድ፣ የሚያስጠነቅቅ የሚከለክል ወይም ሌላ በመንገድ ላይ የሰፈረ የትራፊክ ምልክት ወይም ማመልከቻ በመጣስ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ
 3. በህግ ከተፈቀደው ከፍታ፣ ርዝመት፣ ወይም ስፋት በላይ ተሽከርካሪው ላይ ጭኖ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ
 4. ግራ መንገድ ውስጥ ገብቶ እያሽከረከረ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሠ
 5. አደንዛዥ ዕፅ ወይም መጠጥ ጠጥቶ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሠ
 6. የቴክኒክ ጉድለት ያለበትን ተሽከርካሪ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሠ፡፡

በመጨረሻ የምናገናቸው ሠባተኛ የቅጣት እርከን ላይ የተቀመጡትን የጥፋት አይነቶች ሲሆን ማንኛውም ሠው እነዚህን አይነት ጥፋቶች አጥፍቶ ቢገኝ 7ዐዐ.ዐ0 ብር ቅጣት ይከፍላል፡፡ ጥፋቶቹም እንደሚከተሉት ትዝርዝረዋል፡፡

 1. የቴክኒክ ጉድለት ያለበትን ተሽከርካሪ የትራፊክ ምልክትና ማመልከቻ ጥሶ በማሽከርከር በንብርት ላይ ጉዳት ያደረሠ
 2. የቴክኒክ ጉድለት ያለበትን ተሽከርካሪ በመጠጥ ወይም በአደንዛዥ እጽ ሰክሮ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ
 3. መንጃ ፈቃድ ሣይኖረው ተሽከርካሪ በማሽከርከር በንብርት ላይ ጉዳት ያደረሰ
 4. ተሽከርካሪ እያሽከረከረ በንብረትም ሆነ በሠው ላይ አደጋ አድርሶ ያመለጠ
 5. ለአምቡላንስ ወይም ለእሣት አደጋ ተሽከርካሪ ቅድሚያ ከልክሎ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሠ

እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው ከባድ ጥፋቶችን አጥፍቶ የተገኘ ማንኛውም ሠው በደንቡ መሠረት ተገቢውን የቅጣት ክፍያ ማለትም 7ዐዐ.ዐዐ ብር ይከፍላል፡፡

የትራፊክ ደንብ አንቀፅ 4/4/ እንደሚደነግገው ከሆነ ማንኛውም አሽከርካሪ በተደጋጋሚ ጥፋት ከፈፀመ ከላይ ከዘረዘርናቸው የገንዘብ ቅጣቶች በተጨማሪ የመንገድ ስነ ሥርአት ፈተና ወይም የመሰናክል ፈተና ወይም የከተማ ዉስጥ ማሽከርከር ፈተና በድጋሚ እንዲወስድ በማድረግ ወይም ለተለያየ ጊዜ የሚቆይ የመንጃ ፈቃድ/የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ዕገዳ በማድረግ ወይም የመንጃ ፈቃዱን/የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱን ለዕድሜ ልክ በመንጠቅ ይቀጣል፡፡ የቅጣቱ አፈፃፀምም እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

የግል ተሽከርካሪ አሽከርካሪ

ከሁለት ጊዜ በላይ ከባድ ወይም እጅግ ከባድ የትራፊክ ደንብ ጥፋት የፈፀመ ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ የመንጃ ፈቃዱ ወይም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ተይዞ

 1. ለZስተኛ የጥፋት ሪኮርድ ለ3 ወር ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል
 2. ለአራተኛ የጥፋት ሪኮርድ ለ6 ወር ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል
 3. ለአምስተኛ ጊዜ የጥፋት ሪኮርድ ለ1 አመት ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል
 4. ለስድስተኛ ጊዜ የጥፋት ሪኮርድ ለ2 አመት ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል
 5. ለሠባተኛ ጊዜ የጥፋት ሪኮርድ የመንጃ ፈቃድ/ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ውድቅ ይሆናል፡፡ ሆኖም ከ3 አመት በኃላ አዲስ መንጃ ፈቃድ ሊያወጣ ይችላል፡፡

ከአምስቴ በላይ ማንኛውንም የትራፊክ ደንብ ጥፋት የፈፀመ ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ የመንጃ ፈቃዱ ወይም የአሽከርካሪ ብቅት ማረጋገጫ ፈቃዱ ተይዞ

 1. ለስድስተኛ ጥፋት ረኮርድ የመንገድ ሥነ-ስርዓት ፈተና በድጋሚ እንዲውስድ ይደረጋል
 2. ለሠባተኛው ጥፋት ሪኮርድ የመሠናክል ፈተና በድጋሚ እንዲወስድ ይደረጋል
 3. ለስምንተኛ የጥፋት ሪኮርድ የከተማ ውስጥ ማሽከርከር ፈተና በድጋሚ እንዲወስድ ይደረጋል
 4. ለዘጠነኛ የጥፋት ሪኮርድ መንጃ ፈቃድ / የአሽከርካሪነት ብቃት ማረጋገጫ ውድቅ ይሆናል፡፡ሆኖም ከ6 ወር በኃላ አዲስ መንጃ ፈቃድ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሊያወጣ ይችላል፡፡

የሌላ ተሽከርካሪ አሽከርካሪ

ከZስት ጊዜ በላይ ከባድ ወይም እጅግ ከባድ የትራፊክ ደንብ ጥፋት የፈፀመ ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ የመንጃ ፈቃዱ ወይም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ተይዞ እንደየጥፋት ሪኮርድ ከ6 ወር ጀምሮ እስክ ሁለት /2/ አመት ድረስ ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይደረጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሠባተኛ የጥፋት ሪኮርድ መንጃ ፈቃድ ወይም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ዉድቅ ይሆናል፡፡ሆኖም ከአምስት አመት በኋላ አዲስ መንጃ ፍቃድ/የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ሊያወጣ ይችላል፡፡ይኸው አሽከርካሪ ለስምንተኛ ጊዜ ሪኮርድ ከተያዘበት የመንጃ ፈቃዱ/ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ይሰረዛል፡፡

ከሠባት ጊዜ በላይ ማንኛውም የትራፊክ ደንብ ጥፋት የፈፀመ ከገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ የመንጃ ፈቃድ ተይዞ

 1. ለስምንተኛ የጥፋት ሪኮርድ በድጋሚ የመንገድ ስነስርአት ፈተና  እንዲወስድ ይደረጋል
 2. ለዘጠነኛ የጥፋት ሪኮርድ የመሠናክል ፈተና በድጋሚ እንዲወስደ ይደረጋል
 3. ለአስረኛ የጥፋት ሪኮርድ የከተማ ውስጥ ማሽከርከር ፈተና በድጋሚ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡
 4. ለአስራአንደኛ የጥፋት ሪኮረድ የመንጃ ፍቃድ ወይም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ውድቅ ይሆናል፡፡ ሆኖም ከ1 አመት በኃላ አዲስ መንጃ ፈቃድ ወይም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሊያወጣ ይችላል፡፡

ተጨማሪ ጥያቄ አስተያየት ቢኖርዎት ያነጋግሩን ይጠይቁን

ኢሜይል  ፡-fikadu@ethiopianlaw.com

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንብረት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የካሳ ጠበቃ፣ኢትዮጵያዊ የዉል ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንብረት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የካሳ ጠበቃ… ማግኘት ይችላሉ፡፡