የስራ ስንብት ክፍያ ዋነኛው አላማው በስራ ላይ የቆየ ሠራተኛ አዲስ ስራ ፍለጋ ላይ እያለ ሊደርስበት የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ ነው፡፡ የኘሮቪደንት ፈንድ አላማም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ መመልከት ይቻላል፡፡ ታዲያ አላማቸው አንድ አይነት ከሆነ አሠሪን ሁለት ጊዜ ማስከፈል ፍትሀዊ ነው ማለት ይቻላል? 

በአመልካች በአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ እና በተጠሪ ኤፍሬም ንዋየማርያም መሃከል የተደረገ ክርክርም ይህንን የሚያሳይ ነው፡፡ ጉዳዩ የተጀመረው በፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ሲሆን ይዘቱም ተጠሪ በአመልካች ድርጅት ተቀጣሪ ሆነው ሲሠሩ ቆይተው ስራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ሲለቁ ኘሮቪደንት ፈንድን ጨምሮ የሚገባቸውን ሌሎች ጥቅማጥቅሞች አመልካች የከፈላቸው ቢሆንም የስራ ስንብት ክፍያ ያልከፈላቸው መሆኑን ገልፀው የስራ ስንብት ክፍያ ብርና ይህ ክፍያ ለዘገየበት ደግሞ ተጨማሪ የ3 ወር ደመወዝ አመልካቹ እንዲከፍል ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ 

ጉዳዩን የተመለከተው የመጀመሪያ ፍ/ቤትም ክርክሩን ከመረመረ በኋላ ተጠሪ የኘሮቪደንት ፈንድ የተከፈላቸው መሆኑን ማመናቸው በአዋጅ ቁጥር 484/98 ደግሞ አንድ ሰው ሁለት ጊዜ እንዲከፈለው የሚፈቅድ ስላልሆነ ተጠሪ የስንብት ክፍያ ጥያቄ አይገባቸውም በማለት ወስኗል፡፡ ይግባኝ የቀረበለት ከፍተኛ ፍ/ቤትም የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ በመሻር ተጠሪ የስራ የስንብት ክፍያ ሊከፈላቸው ይገባል በማለት ወስኗል፡፡ 

የሰበር ችሎትም የአመልካችን አቤቱታ ተመልክቶ የግራ ቀኙን ክርክር እልባት ለመስጠት አግባብነት ያለውን የህግ ድንጋጌና መንፈስ ጋር መርምሯል፡፡ በዚህም መሠረት በጉዳዩ አግባብ የሆነው ህግ የአሠሪና ሠሪተኛ ጉዳይ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/1998 ሲሆን በአንቀጽ 2(ሰ) ላይ እንደተመለከተውም “የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ ሰራተኛ የኘሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ወይም የጡረታ መብት የሌለው ሲሆንና …” 

ከዚህ ድንጋጌም በቀላሉ መገንዘብ የሚቻለው የኘሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ያለው ሠራተኛ የስራ ውሉ ሲቋረጥ የስራ ስንብት ክፍያ ከአሠሪው የማግኘት መብት የሌለው መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ሕግ አውጪው የኘሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ የሆነ ሠራተኛ የስራ ውሉ ሲቋረጥ ከአሰሪው የስራ ስንብት  መጠየቅ መብቱን የነፈገው ከላይ የተገለፀውን አሠሪን ሁለት ጊዜ እንዳይከፍል በመጠበቅ ነው ተብሎ ከማሰብ ውጪ ሌላ ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ 

 

ከዚህም የተነሳ ተጠሪ የኘሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ መሆኑን ያመኑ ካልሆነ የስራ ስንብት ክፍያም ሊከፈላቸው ይገባል በማለት ከፍተኛው ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ የሰበር ችሎት መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት አለበት በማለት ሽሮታል፡፡ ስለዚህም የኘሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ የሆነ ሠራተኛ የስንብት ክፍያ መጠየቅ እንደማይችል ከዚህ መረዳት እንችላለን፡፡ 

ተጨማሪ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካለዎት  ያግኙን

ኢሜይል  ፡-fikadu@ethiopianlaw.com 

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ታክስ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የወንጀል ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንብረት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የካሳ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የፓተንት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኮፒራይት ጠበቃ… ማግኘት ይችላሉ፡፡