የአንድ ሰራተኛ የስራ ውል መቼ ሊቋረጥ እንደሚችል ማወቅ ይፈልጋሉ; እንግዲያውስ ምክኒያቶቹን ከዚህ እንደሚከተለው አስቀምጠንልዎታል፡፡ የስራተኛና አሰሪ ግንኙነትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ አግባብነት ያለው ህግ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 ነው፡፡ በዚህ አወጅ መሰረትም በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ተጀምሮ የነበረው የስራ ውል በተለያዩ መንሰኤዎች ሊቋረጥ ይችላሉ፡፡ የአሰሪና የሰራተኛ አዋጅ የስራ ግንኙነት የሚቋረጥባቸው ምክኒያቶች በሶስት አበይት መደቦች ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ እነርሱም

 

  1. በአሰሪው ወይም በሰራተኛው ተነሣሽነት፣
  2. በህግ በተደነገገው መሠረት ወይም፡
  3. በህብረት ስምምነቶች መሰረት ናቸው

ይህ ጽሁፍም ትኩረት የሚያደርገው የሰራተኛና አሰሪ የስራ ግንኙነትን የሚያቋርጥባቸው መንገዶች በኢትዮጵያ ህግ ምን እንደሚመስሉ ነው፡፡ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ 377/96 መሠረት አሰሪው በሰራተኛው ጠባይ ወይም የሰራተኛውን የመስራት ችሎታ ከሚመለከቱ ግልጽ ሁኔታዎች ወይም ከድርጅቱ አቋም ወይም የስራ እንቅስቃሴ ባላቸው ምክንያቶች ብቻ ሊያቋርጥ ይችላል፡፡

ከዚህ በመቀጠል አሰሪው የስራ ውሉን የሚያቋርጥባቸውን ህጋዊ መንገዶች እናያለን፡፡

ሀ. ያለ ማስጠንቀቂያ የስራ ውል ማቋረጥ

የአንድ ሰራተኛ የሰራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ሊቋረጥ የሚችለው ሰራተኛው ከዚህ በታች የተዘረዘሩት አይነት ከባድ ጥፋቶች ፈጽሞ ሲገኝ ነው፡፡ እነርሱም

ü      ያለበቂ ምክንያትና ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው ተደጋጋሚ የሆነ የሰራ ሰዓት አለማክበር፣

ü      ያለበቂ ምክንያት ለተከታታይ 5 ቀናት ወይም በወር 10 ቀናት ወይም በዓመት ለ30 ቀናት ከስራ መቅረት፣

ü      የማታለል ወይም የማጭበርበር ተግባር መፈፀም፣

ü      የአሰሪውን ንብረት ወይም ገንዘብ አለአግባብ መጠቀም፣

ü      ከተወሰነው የምርት ጥራትና መጠን በታች የስራ አፈፃፀም ሰራተኛው ሲፈጽም፣

ü      ሰራተኛው በወንጀል ጠፋተኛ ሆኖ መገኘትና በጥፋቱ ምክንያት ለያዘው ስራ ብቁ ሆኖ አለመገኘት፣

ü      በስራው ቦታ አምባጓሮ ወይም ጠብ  አጫሪነት ተጠያቂ መሆን፣

ü      ህይወትና ንብረትን አደጋ ላይ የሚጥል ድረጊት ሆነ ብሎ በስራ ቦታ መፈፀም፣

ü      አሰሪው በግልጽ ሳይፈቅድ ከስራ ቦታ ንብረት መውሰድ፣

ü      በስራ ላይ ስክሮ መገኘት፣

ü      ህግ ቢያስገድድ ወይም አሰሪው በበቂ ምክንያት ሲጠይቅ ከHIV ምርመራ በስተቀር የጤና ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆን፣

ü      ስለደህንነት ጥበቃና ስለ አደጋ መከላከል የወጡ የስራ ደንቦችን አለማክበርና አስፈላጊ የሆኑትን የአደጋ መከላከያ ጥንቃቄዎች ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆን፣

ü      ያለማስጠንቀቄያ የስራው ውል ለማቋረጥ ያስችላሉ ተብለው በህብረት ስምምነቶች የተወሰኑ ሌሎች ጠፋቶችን መፈፀም፣

ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች አሰሪው የስራ ውልን በሚያቋርጥበት ጊዜ የስራ ውሉ የተቋረጠበትን ምክንያት በ30 ቀናት ውስጥ ለሰራተኛው በጽሁፍ መግለጽ ይገባዋል፡፡

 

ለ. በማስጠንቀቂያ የስራ ውል ስለማቋረጥ

የሚከተሉት ምክንያቶች አሰሪው በማስጠንቃቂያ የስራ ውልን ለማቋረጥ በቂ ምክንያቶች ሊሆኑት ይችላሉ፡-

ü      የስራተኛው የስራ ችሎታ ቀንሶ ሲገኝ ይህንንም ለማሻሻል አሰሪው ያዘጋጀለትን የትምህርት ዕድል ሳይቀበል ሲቀር፣

ü      ሰራተኛው በደረሰበት የጤና መታወክ ወይም የአካል ጉዳት ሳቢያ ግዴታውን ለዘለቄታው ለመወጣት ሳይችል ሲቀር፣

ü      ድርጅቱ ወደ ሌላ ቦታ ሲዘዋወር ሰራተኛው አብሮ ለመዛወር ፍቃደኛ ሳይሆንም ሲቀር፣

ü      ሰራተኛው የያዘው የስራ መደብ በበቂ ምክንያት ሲሰረዝና ሰራተኛውን ወደ ሌላ ስራ ማዛወር የማይቻል ሆኖ ሲገኝ፣

በአሰሪው የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ለሰራተኛው በእጁ መስጠት አለበት፡፡ ሰራተኛውን ማግኘት የማይቻል ከሆነ ወይም ሰራተኛውን ፈቃደኛ ካልሆነ ማስጠንቀቂያው ግልጽ በሆነ የማስታወቂያ ሰሌዳ ለ10 ተከታታይ ቀናት ይለጠፋል

የማስጠንቀቂያ ጊዜ

የማስጠንቀቂያ ጊዜ ማለት አንድ ሰራተኛ የስራ ውሉ በማስጠንቀቂያ ለሚቋረጥባቸው የጥፋት አይነቶች የሚሰጠው የማስጠንቀቂያ ቀናት መጠን ነው፡፡ አሰሪው ለሰራተኛው የሚሰጠው የማስጠንቀቂ ጊዜ እንደሚከተለው ይወስናል፡፡

ü      የሙከራ ጊዜውን የጨረሰና እስከ አንድ ዓመት ያገለገለ ሰራተኛን በሚመለከት ረገድ የአንድ ወር የማስጠንቀቂያ ጊዜ፣

ü      ከአንድ ዓመት በላይ እስከ ዘጠኝ ዓመት ያገለገለ ሰራተኛን በሚመለከት ረገድ የሁለት ወር የማስጠንቀቂያ ጊዜ፣

ü      ከዘጠኝ ዓመት በላይ ያገለገለ ሰራተኛ በሚመለከት ረገድ 3 ወር የማስጠንቀቂያ ጊዜ፣

ü      የሙከራ ጊዜ ጨርሰውና በቅነሣ ምክንያት የስራ ውላቸው የሚቋረጥባቸውን ሰራተኞች በሚመለከት 2 ወር የማስጠንቀቂያ ጊዜ፣

ሐ. የሰራተኞች ቅነሣ

የሰራተኛ ቅነሳ ለማድረግ መሟላት ያለባቸው ምክንያቶች

ü      አሰሪው በሚያመርታቸው ምርቶች ወይም በሚሰጣቸው አገልገሎቶች ተፈላጊነት መቀነስ ምክንያት የድርጅት የስራ እንቅስቃሴ በመቀዝቀዙና ትርፍ እየቀዘቀዘ በመሄዱ የሰራተኞችን ቅነሣ ማድረግ አስፈላጊ ሲሆን፣

ü      ምርታማነትን ለማሣደግ አዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ሲባል የሚደረግ ቅነሣ፣

ü      ሰራተኞች የተሰማሩባቸውን ሰራዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ በቀጥታና ለዘለቄታው የማያስቆም የሰራተኞች ቅነሳ የሚያስከትል ሁኔታ ሲከሰት፣

ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ሲከሰቱ

ü      ቁጥራቸው ከድረጅቱ ሰራተኞች ቢያንስ ከመቶ አስር የሚያህለውን ወይም

ü      የሰራተኞች ቁጥር ከ20-50 በሆነበት ድረጅ ቢያንስ 5 ሰራተኞችን የሚመለከት ከአስር ተከታታይ ቀናት ላላነሰ ጊዜ የሚቆይ የሰራተኞች ቅነሣ ነው፡፡

አሰሪው ከሰራተኞች ማህበረ ወይም ተወካይ ጋር በመመካከር ከፍተኛ የምርት ውጤት የሚያሳዩ ሰራተኞችን በስራቸው ላይ እንድቆዩ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡

ተመሳሳይ የስራ ችሎታ ያላቸውና ተመሳሳይ የምርት ውጤት የሚያሣዩ ሰራተኞች ሲኖሩ ቅነሣው በመጀመሪያ ደረጃ የሚመለከታቸው ሰራተኞች

ü      በድርጅቱ ለአጭር ጊዜ ያገለገሉ ሰራተኞች

ü      አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጥገኞች ያላቸው ሰራተኞች

ü      በድርጅቱ ሳሉ በሰራ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰራተኞች፣

ü      የስራተኞች ተጠሪዎች፣

ü      ነፍሰጡር ሴቶች፣

. ሰራተኛው የስራ ውሉን ራሱ ሲያቋርጥ

ሌላው የስራ ውል ሊቋረጥ የሚችልበት ምክኒያት ሰራተኛው የስራ ውሉን በራሱ ፈቃድ ሲያቋርጥ ሲሆን የስራተኛው የአገልግሎት ዘመን ግምት ውስጥ ሳይገባ ማንኛውም የሙከራ ጊዜውን የጨረስ ሰራተኛ የስራ ውሉን ለማቋረጥ የአንድ ወር የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት አለበት፡፡

ተጨማሪ ጥያቄ አስተያየት ቢኖርዎት ያነጋግሩን ይጠይቁን

ኢሜይል  ፡-fikadu@ethiopianlaw.com

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ኢትዮጵያዊ የስራ ፈቃድ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ጠበቃ… ማግኘት ይችላሉ፡፡