በፍትሀብሔር ስነስርዓት ህጋችን አንቀፅ 223 መሰረት አንድ ከሳሽ ከሚያቀርበው የክስ ማመልከቻ ጋር በክሱ መስማት ወቅት ለጉዳዩ ማስረጃ ይሆኑኛል የሚላቸውን የሰውም ሆነ የፅሑፍ ማስረጃዎችን በተመለከተ ማንኛውም ተከራካሪ ወገን ከአቤቱታው ጋር በማያያዝ ወይም ከቀን ቀጠሮ በፊት ወይም በመጀመሪያው ቀን ቀጠሮ ካልቀረበ በቀር ማስረጃው ሊቀርብ ወይም ይቅረብልኝ ተብሎ ሊጠየቅ እንደማይቻል ተመልክቷል፡፡

ታዲያ ይህ ማለት ማንኛውም አይነት ማስረጃ በትክክለኛው አካሔድ ካልቀረበ በፍ/ቤቱ ተቀባይነት አያገኝም ማለት ነው የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በጥር 14 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የሰበር ውሳኔ የተሰጠበት መዝገብ ግን ማስረጃን ለፍትሃዊነት ተገቢ ነው ብሎ ፍርድ ቤት ካመነበት ማስረጃን መቀበል እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡

ጉዳዩ በአመልካች ህድአት ፍስሃፅዮን እና በተጠሪ አልማዝ ተረፈ እና በአ/አ ከተማ መስተዳደር ዞን 4 ፅ/ቤት መሃከል ሲሆን ከሳሽ በአ/አ ከተማ ወረዳ 16 ቀበሌ ዐ3 ውስጥ የሆነውን ቤት ለወ/ሮ አልማዝ ከታህሳስ 23 ቀን 1991 ዓ.ም ጀምሮ ማከራየታቸውን ገልፀው ተጠሪዋ ያለባቸውን የቤት ኪራይ ከፍለው ቤቱን እንደነበረ አድርገው ለአመልካች እንዲያስረክቡ የአ/አ መስተዳድር ዞን 4 ጽ/ቤትም ቤቱን ያለ አግባብ ለ1ኛ ተጠሪ በብር 355,000.00(ሦስት መቶ ሃምሳ አምስት ሺህ ብር) ሸጦ በመገኘቱ ቤቱን የሚሰጠውን የአገልግሎት ኪራይ እንዲከፍልና ቤቱን ለቀው እንዲያስረክቧቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከተው ፍ/ቤትም የሽያጭ ውሉ ህገወጥ ነው በማለት ተከሳሾች ቤቱን እንዲያስረክቡ ከ28/12/93 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም የቤቱን ኪራይ ባልተነጣጠለ ሃላፊነት እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡ ይህን ውሳኔ በመቃወም ተጠሪዎች ይግባኛቸውን ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርበው ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን ከመረመረ በኋላ ቤቱ የተመዘገበው በጄነራል ገብረአብ ወልዳይ ስም በመሆኑ አመልካች በቤቱ ላይ መብት ያላቸው ስለመሆኑ አላስረዱም በማለት የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ሽሮታል፡፡

 

አመልካችም መሠረታዊ የህግ ስህተት ተፈፅሟል በማለት ይግባኛቸውን ለሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም በአጭሩ አመልካች የሟች ሚስት መሆኔን አሳውቄና ማስረጃ ለፍ/ቤቱ ቀርቦ እያለ አለመታየቱ አግባብ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ማስረጃ በክርክሩ ሒደት ተያይዞ ያልቀረበና የሚያውቁት መሆኑን ተጠሪዎች ገልፀው አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ የክርክሩ ሒደት የሚያሳየው አመልካች የሟች ብርጋዴር ጄኔራል ገብረአብ ወልዳይ ሚስትነት እና የልጆቻቸው ወራሽነት በፍ/ቤቱ ሰነድ ያልተገለፀ መሆኑን ነው፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎትም ሁኔታውን ተመልክቶ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 345 ድንጋጌ የይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት በራሱ አስተያየት ተገቢ ሆኖ ሲያገኘው ማናቸውም ዓይነት ሰነድ ወይም ይኸው ወይም ሌላ አይነት ማስረጃ በተጨማሪነት እንዲቀርብለት የማዘዝ ህጋዊ ስልጣን ያለው ስለመሆኑ ያሳያል፡፡ ነገር ግን አመልካች ሚስትነታቸው አረጋግጠዋል በማለት በውሳኔው ግለባጭ መኖሩን የሰጠው የፌደራሉ የመጀመሪያ ፍ/ቤት አመልካች የተጠቀሰው የፍ/ቤት መዝገብ ከሚገኝበት ፍ/ቤት ጉዳዩን ባዩት ፍ/ቤቶች አነሳሽነት ጭምር ሊቀርብና ተጠሪዎች በሰነዱ ይዘት የሚያቀርቡት ክርክር ከታየ በኋላ ውሳኔ መስጠት በተገባ ነበር በማለት በስር ፍ/ቤቶች የተሰጡትን ውሳኔዎች ሙሉ በሙሉ ሽሯቸዋል፡፡

ተጨማሪ ጥያቄ አስተያየት ቢኖርዎት ያነጋግሩን ይጠይቁን

ኢሜይል  ፡-fikadu@ethiopianlaw.com

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢንቨስትመንት ጠበቃ፣ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ የጉዲፈቻ ጠበቃ፣ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ የፓተንት ጠበቃ፣ የኮፒራይት ጠበቃ፣ የታክስ ጠበቃ፣ የባንክ ጠበቃ፣ የኢንሹራንስ ጠበቃ፣ የፍቺ ጠበቃ፣ የቅጥር ውል ጠበቃ፣ የስራ ውል ጠበቃ፣ የውርስ ጉዳይ ጠበቃ፣ የኑዛዜ ጠበቃ፣ የቤተሰብ ጠበቃ፣ የንብረት ጠበቃ፣ የካሳ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ… ማግኘት ይችላሉ፡፡