በፍ/ብ/ሕ አንቀጽ 665(2) መሠረት “የኑዛዜ ቃል አፈፃፀሙም የማይቻል እንደሆነ እንደዚሁ ፈራሽ ነው፡፡” በማለት የደነገገ ሲሆን ይህን ነጥብ አስመልክቶም ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡

ጉዳዩ በስር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የቀረበው በአሁኑ አመልካች ሲሆን ጥያቄያቸውም፤ ሟች ባላምባራስ ዘውዴ ደምሴ በመስከረም 26/1984ዓ.ም ያደረጉት ኑዛዜ በፍ/ቤት ፀድቆላቸው የኑዛዜ ወራሽነታቸው ተረጋግጦ እንደሰጣቸው ነው፡፡

ተጠሪዎቹ በተቃዋሚነት ቀርበው አንደኛና ሁለተኛ ተጠሪዎች ሟች መስከረም 26 ቀን 1989 ዓ.ም እና ግንቦት ዐ5 ቀን 1988 ዓ.ም ያደረጋቸው ኑዛዜዎች ሟች የካቲት 12 ቀን 1989 ዓ.ም ባደረጉት ኑዛዜ የተሻሩና የተተኩ በመሆኑ ኑዛዜው ሊፀድቅ አይገባም በማለት የተከራከሩ ሲሆን ሶስተኛው ተጠሪ ግን ለብቻቸው ባቀረቡት መልስ በአመልካች ጥያቄ ላይ ተቃውሞ የሌላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ለቀረበለት ጉዳይ እንደሚከተለው በማተት ውሳኔውን ሰጥቷል፡፡ ሟች ከመስከረም 26 ቀን 1984 ዓ.ም በኋላ ሁለት የተለያየ ኑዛዜዎች ማድረጋቸውን፣ አንደኛና ሁለተኛ ተጠሪዎች ደግሞ ሟች የካቲት 12 ቀን 1989 ዓ.ም ያደረጉት ኑዛዜ እንዲፀድቅላቸው ጥያቄ አቅርበው የአሁኗ አመልካች እና የአሁኑ ሦስተኛ ተጠሪ በተቃዋሚነት ቀርበው ይኸው ኑዛዜ በመ/ቁ 1169 የካቲት 10 ቀን 1997 ዓ.ም በፍ/ቤቱ መጽደቁን፤ መስከረም 26 ቀን 1984 ዓ.ም በተደረገው ኑዛዜ ሟች በወረዳ 3 ቀበሌ 44 የቤት ቁ.220 የሆነውን ቤታቸውን ለወ/ሮ የውብዳር አልማዝ ዘውዴ መስጠታቸውን በመከጡሪ ከተማ ያለውንም ቤት ወ/ሮ አልማዝ ዘውዴ በራሷ ገንዘብ የገዛችው መሆኑን ገልፀው ማንም እንዳይጠይቃት የተናዘዙ መሆኑን ሆኖም እነዚህን ንብረቶች ወ/ሮ እቴቱ ዘውዴ እንዲወስዱ የካቲት 12 ቀን 1989 ዓ.ም ባደረጉት ኑዛዜ መናዘዛቸውን ዘርዝሮ መስከረም 26 ቀን 1984 ዓ.ም ተደረገ የተባለው ኑዛዜ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 859(2) መሠረት በሟች ተለውጧል የሚል ምክንያት በመያዝ የአመልካችን የኑዛዜ ይጽደቅልኝ ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

በዚህ ውሳኔ የአሁኗ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርበው ይኸው ፍ/ቤት ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡

የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም በዚሁ የበታች ፍ/ቤቶች ውሳኔ ባለመስማማት ለመለወጥ ነው፡፡

አመልካች ሟች ኑዛዜ ያደረጉበት ንብረት የግላቸው ባልሆነው መሆኑን በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 865(2) መሠረት ሊፈፀም የማይችል መሆኑን እና ሌሎች በበታች ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚልባቸውን ምክንያት በመዘርዘር የበታች ፍ/ቤቶች ውሳኔ ተሽሮ ሟች በ26/ዐ1/84 ዓ.ም ያደረጉት ኑዛዜ ፀድቆ እንዲወሰንላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎችም ሟች ኑዛዜ ያደረጉበት ቤት በግል ገንዘባቸው የተገዛ፤ የካቲት 12 ቀን 1989 ዓ.ም የተደረገውን ኑዛዜ አመልካች የተቀበሉት መሆኑን በኮ/መ/ቁ 463 የተደረገው ክርክር እንደሚያሳይና ይኸው ኑዛዜ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 895(3) መሠረት ተቀባይነት ያለው መሆኑን በመዘርዘር መልሳቸውን አቅርበዋል፡፡ ሦስተኛ ተጠሪ በበኩላቸው ሟች አመልካችን ከውርስ የሚነቅሉበት አንዳችም ምክንያት ሳይኖር መንቀላቸውና በአመልካች ስም የሚታወቀውን ቤታቸውን የሟች አስመስለው በኑዛዜ ለሌላ አሳልፈው መስጠታቸው ያላግባብ መሆኑን በመዘርዘር የመስከረም 26 ቀን 1984 ዓ.ም ኑዞዜ ቢፀድቅ ተቃውሞ የሌላቸው መሆኑን ገልፀው ተከራክረዋል፡፡

የሰበር ፍ/ቤቱም አቤቱታው ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው  መርምሮታል፡፡ 

ሟች በመከጡሪ ከተማ 01 ቀበሌ ይገኛል በተባለው ቁጥሩ 139 የሆነውን ቤት አስመልክቶ አደረጉ የተባለው ኑዛዜ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባ ነው ካለ በኋላ በየካቲት 12 ቀን 1989 ዓ.ም ኑዛዜ አመልካች የክርክሩ ተካፋይ በሆኑበት ሂደት በፍ/ቤት የፀደቀ ህጋዊ ፎርማሊቲውን የጠበቀ መሆኑ አጠያያቂ አለመሆኑንም ገልፆል፡፡

ታዲያ የኑዛዜው ሕጋዊ ፎርማሊቲ አጠያያቂ ካልሆነ ሌላ ሊታይ የሚገባ ኑዛዜውን ዋጋ አልባ የሚያደርግነገር እና ምን አለ?

ሰበር ፍ/ቤት የኑዛዜው ሕጋዊ ፎርማሊቲ አጠያያቂ ካልሆነ መታየት ያለበት የኑዛዜው ይዘት ነው በማለት ሟች ባደረጉት ኑዛዜ በሙከጡሪ ከተማ ይገኛል የተባለውን ቁጥሩ 139 የሆነው ቤት ከአመልካች ውጪ ባሉት ወራሾች እንደሚገባ ዘርዝረው የማከፋፈላቸውን ሕጋዊነት ከፍ/ብ/ሕ/ቁ. 865(2) እና ተዛማጅነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ተመልክቶታል፡፡

  1. ኑዛዜ በባሕሪይው ተራ የሐሳብ መግለጫ ቢሆንመ በተናዛዥ በግሉ ብቻ ሊፈፀም የሚገባው ተግባር ነው፡፡
  2. በተለይም ደግሞ ኑዛዜ በይዘቱ ንብረትን ከማስተላለፍ ተግባር ጋር የተያያዘ ሲሆን ሕጋዊ ጥበቃ የሚደረገውም ተናዛዡ የራሱ የሆነውን ሕጋዊ ንብረት በማስተላለፍ ሕጋዊ ኑዛዜ አድርጎ ሲገኝ ስለመሆኑ የውርስ ሕግ ድንጋጌዎች ያሳያሉ፡፡
  3. ተናዛዥ ህጋዊ ንብረቱ ባልሆነው ላይ ኑዛዜ ቢያደርግና ይኸው ኑዛዜ በፍ/ቤት ቢፀድቅ የኑዛዜ ሰነዱ ዋጋ የሚያገኝበት ምክንያት የለም በማለት ከላይ የተጠቀሰውን የሕግ አንቀጽ በመጠቀም በጉዳዩ ላይ በመዝገብ ቁ. የሰ/መ/ቁ. 32817 በ11/10/2001 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
  4. በመከጡሪ ከተማ ውስጥ ይገኛል የተባለው ቤት ሟች ባደረጓቸው ኑዛዜዎች ላይ የሰፈረ መሆኑ እንደተጠቀሰው ሆኖ በ02/01/84 ዓ.ም በተደረገ የቤት ሽያጭ ውል አመልካች የገዙት መሆኑ በውጫሌ ፍ/ቤት በመ.ቁ. G/F/4ዐ28/89 በቀን ዐ7/04/901 በሰጠው ውሳኔ የተረጋገጠ በመሆኑ አከራካሪው ቤት ሕጋዊ ባለቤት አመልካች እንጂ ተናዛዥ አይደሉም፡፡

ይህንንም ቤት በተመለከተ ማች ያደረጉት የኑዛዜ ሰነድ ዋጋ ሊሰጠው የማይገባ ስለሆነ ፈራሽ ነው፤ ቤቱ የአመልካች የግል ቤት ነው በማለት የበታች ፍ/ቤት የሰጡትን ውሳኔዎች በማሻሻል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ የምንገነዘበው ነገር ተቃዋሚዎች ተሳታፊ በሆኑበት መዝገብ ህጋዊነቱ በፍ/ቤት የፀደቀ/የተረጋገጠ ኑዛዜ ሕጋዊ ፎርማሊቲውን የጠበቀ ቢሆንም እንኳ ኑዛዜ አድራጊው የግል ንብረቱ ያልሆነ ንብረት አስመልክቶ በውርስ ለማስተላለፍ የሚያደርገው ኑዛዜ ሊፈፀም የማይችል ዋጋ አልባ ፈራሽ ሊሆን የሚገባ ነዛዜ መሆኑን ኑው፡፡

ተጨማሪ ጥያቄ አስተያየት ቢኖርዎት ያነጋግሩን ይጠይቁን

ኢሜይል ፡-fikadu@ethiopianlaw.com

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የውርስ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የፍቺ ጠበቃ፣ … ማግኘት ይችላሉ፡፡